Home » የኢሳት አማርኛ ዜና » መንግሰት የኢንተርኔት ድረገጾችን እና ብሎጎችን እንደሚያፍን በይፋ አመነ

መንግሰት የኢንተርኔት ድረገጾችን እና ብሎጎችን እንደሚያፍን በይፋ አመነ

ታህሳስ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አንዳንድ የኢንተርኔት ድረገጾች እና ብሎጎች በኢትዮጽያ እንደሚታገዱ የኢንፎርሜሽን ደህንነት ኤጀንሲ ዋና
ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ በይፋ አረጋገጡ፡፡
ብ/ጄኔራሉ ሰሞኑን ለንባብ ከበቃው መንግስታዊው “ዘመን” መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንዳረጋገጡት
አንዳንድ አስጊ ናቸው ያሏቸውን የኢንተርኔት ድረገጾችና ብሎጎችን ማገድ የኤጀንሲው ዋንኛ ስራ አለመሆኑን፤ ነገር
ግን በመርህ ደረጃ መደረግ አለባቸው ብሎ ማስቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡“ለዚህ ደግሞ ቴሌ እንዲያጣራቸው አቅም
የመገንባት ስራ እንሰራለን፡፡ከተቻለ ደግሞ ከሃይማኖት፣ከዘር፣ከሽብርተኝነት፣ከሕዝብ ሞራል ጋር የተያያዙ ድረገጾች
ወደ ኢትዮጽያ እንዳይገቡ ጥረት ይደረጋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“የሃይማኖት አክራሪነት አንድ ስጋት ነው፡፡ከዚያ አልፎ ሽብርተኝነት አለ፡፡ሕዝቡ በስነልቦና እንዲሸበር
ፍርሃት፣ጭንቀት፣አለመተማመን እንዲሰፋ፣ ወጣቱ በሙሉ አቅሙ ወደ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ እንዳይገባ የሚያደርጉ
ኃይሎች አሉ ” ያሉት ብ/ጄኔራሉ  “ይህን ለመቆጣጠር ኢንተርኔትን መሰረት ያደረገ የመከላከያ አቅም መገንባት
ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ብ/ጄኔራሉ በዚሁ ቃለምልልሳቸው መረር ብለው “የኢትዮጽያ ቴሌኮምኒኬሽን የኀብረተሰቡን ሰላም የሚያጠፉ ዌብሳይቶችን
የመቆጣጠር አቅም ሊኖረው ይገባል፡፡መርሁ ይህ ነው፡፡ለኀብረተሰቡ የሰላምና የልማት አጀንዳ እንቅፋት ሊሆኑ
የሚችሉ የመቆጣጠር ብቃት አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡
“ስርዓት ያልተበጀለት ኢንተርኔት ጉዳቱ ሰፊ ነው” የሚሉት ብ/ጄኔራል ተክለብርሃን “ሕገመንግስቱን ም ሆነ የሕዝቡን ሰላም
የሚጻረሩ እንቅስቃሴዎች ሊፈቀድላቸው አይገባም” ብሎ አስቀምጧል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጽያ መንግስት በኢንተርኔት ድረገጾች እና ብሎጎች ላይ አፈና በማድረግ የዜጎችን ኀሳብን በነጻ የመግለጽ
ነጻነት የሚጻረሩ ሕገወጥ እርምጃዎችን ይወስዳል በሚል የሚቀርብበትን ተደጋጋሚ ክሶች፤ መሰረተ ቢስ ናቸው በሚል
ሲያጣጥል መቆየቱ አይዘነጋም፡፡