Home » የኢሳት አማርኛ ዜና » አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር፣ ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ እና ሦስት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የፍትህ ስርዓቱንና አቶ መለስ በፓርላማ ያደረጉትን ንግግር ተቹ

አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር፣ ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ እና ሦስት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የፍትህ ስርዓቱንና አቶ መለስ በፓርላማ ያደረጉትን ንግግር ተቹ

ኢሳት ዜና:- ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  ምሁር፤አንድ  ዳኛ ህገ-መንግስቱ  ውስጥ በተቀመጠው  መሰረት  የዳኝነት ነፃነቱን  እንዴት ያለ ተፅዕኖ ሊገብር ይችላል?” የሚለውን ጉዳይ ለማየት፤ “ዻኛው ማነው?”፣ዳኛ ለመሆን የሚያስችሉት መስፈርቶችስ ምንድናቸው? የሚለውን የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ማየት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የዴሞክራሲ ሥርዓት በሚከተሉ  አገሮች የዳኝነት አካል ሲዋቀር  ዜጐች  በተለያየ  መንገድ እንደሚሳተፉ፤ በዳኝነት  የሚሾሙት  ሰዎችም ዕድሜያቸው በሰል  ያለና  ከፍተኛ  ልምድ ያካበቱ  መሆናቸውን  የሚናገሩት
እኚሁ ምሁር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን  በአብዛኛው  ሹመት  ላይ የሚወጡት  ዳኞች  ከሥርዓቱ  ጋር  የሚስማሙ  ከመሆናቸው  በተጨማሪ፣ አንድ ሰው በ25 ዓመቱ  ዳኛ እንዲሆን መፈቀዱ፤ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ችግር ማስከተሉን ይገልጻሉ፡፡

እንዲሁም ኢትዮጵያ  ውስጥ በዳኝነት አስተዳደር ጉባዔ  ላይ  የሚሳተፉት ሰዎች  ከፖለቲካ  የፀዱ ናቸው ብሎ ለመናገር  እንደማይቻል የገለጹት ምሁሩ፤ የአገሪቱ  ፓርላማ  የተለያየ  ሕግ ሲያፀድቅ አስተያየት የሚሰጡት እነዚህ ሰዎች መሆናቸውም፤ በዳኝነት ነፃነት ላይ የራሱን ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ይናገራሉ፡፡  ብቸኛው የተቃዋሚ  ፓርቲ  የፓርላማ  አባል አቶ ግርማ  ሰይፉ  በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከምርጫ  ቦርድ ቀጥሎ በአሠራር ላይ ችግር የሚታይበት ተቋም፤ የፍትሕ  አካሉ  መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱን ሊቀንሱ የሚችሉ ነገሮች በአስፈጻሚው አካል ሲከወኑ ‹‹አይሆንም!›› ብሎ የሚቃወም  የፍትሕ ሥርዓት  ሊኖር  እንደሚገባ የሚናገሩት  አቶ ግርማ፣ የኢትዮጵያ  የፍትሕ  ሥርዓት  ግን  ተቃራኒው  ሥልጣኑ  በአስፈጻሚው  አካል  ተነጥቆ  ለአገር  ውስጥ  ገቢ፣ ለባንኮች፣ ለመንግሥት ቤቶች  ኤጀንሲና  ለሌሎች  ተቋማት ሲሰጥ፤ ‹‹አሜን›› ብሎ በመቀበሉ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየተዳከመ  መምጣቱን ያስረዳሉ፡፡

ዳኞች  ከፖለቲካ ንክኪ  ነፃ  አለመሆናቸውም ፤በፍትሕ ሥርዓቱ  ላይ ችግር መፍጠሩን  አቶ ግርማ  ተናግረዋል፡፡‹‹ዳኞች  የፖለቲካ  ንክኪ እንዳላቸው  መጠራጠር  አያስፈልግም፤ ሲቪያቸውን  ማየት  በቂ ነው፤ ሲቪል  ሰርቪስ  ማንን  እንደሚያሰለጥን ይታወቃል፤›› ያሉት አቶ ግርማ፣  ከሲቪል  ሰርቪስ  የሚመረቁ  ዳኞች  በአንድ  ወቅት  የፓርቲ  አባል  ወይም  ታጋይ  የነበሩ  በመሆነቸው ፤”ነፃ ናቸው” ለማለት  እንደሚያስቸግር  አመልክተዋል፡፡
ሥራ አስፈጻሚው  በፍትሕ   አካላት  ላይ   ከሚያደርገው   ጣልቃ   ገብነት   በተጨማሪ፣  በፍርድ  ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ የመንግሥት ሚዲያና ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚሰጡት አስተያየት በዳኞች ውሳኔ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የተናገሩት አቶ ግርማ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሰሞኑን በፓርላማ ተገኝተው በተጠርጣሪዎች ላይ ‹‹አሳማኝ ማስረጃ አለን›› ብለው መናገራቸው ጥፋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅሩና  እኔም  ብናገር  ተፅዕኖ የማልፈጥርበት ምክንያት የለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ እንደሚለው ፤አንድ ሰው ጥፋተኛ መሆኑ  እስካልተረጋገጠ  ድረስ  ነፃ  ሆኖ የመታሰር መብት አለው፡፡ “ነፃ ነው” ብሎ ማሰብ ትክክል ነው፡፡ ጥፋቱ፦”ወንጀለኞች ናቸው”ብሎ ማሰብ ነው  ብለዋል፡፡
በትግርኛ ቋንቋ የሚዘጋጀው ‹‹ጥሕሎ›› መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ በበኩሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በጋዜጠኞች ላይ የሰጡት ማስፈራሪያና በተጠርጣሪዎች ላይ የሰጡት አስተያየት፤ ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ነው ብሏል።
‹‹እነዚህ ሰዎች በፍርድ ቤት የተረጋገጠ ወንጀል እስካልተገኘባቸው ድረስ ንፁኅን ናቸው ነው እያልን ያለነው፡፡ እርሳቸው ግን እርግጠኛ ሆነው አሸባሪ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ይኼ በዳኞች ላይ የሚያሳድረውን ፖለቲካዊ ተፅዕኖ መገመት አያቅትም፤›› ይላል- ዮናስ፡፡

ጋዜጠኛ ዮናስ እንደሚለው፣ ዳኞቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ የተናገሩትን ከመወሰን ውጪ ወደ ኋላ የሚሉ አይሆንም፡፡ በኢትዮጵያ በሕግ አስፈጻሚው፣ በሕግ ተርጓሚውና በሕግ አውጭው መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት አለመኖሩን የሚናገረው ዮናስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሦስቱንም አካላት ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን  አመልክቷል-‹‹ራሳቸው ሕግ አርቃቂ፣ ሕግ አውጪና ፈራጅ ሆነዋል፤›› በማለት፡፡
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ሊቀመንበርና የመድረክ ፓርቲ አመራር አባል ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው፣ በአሸባሪነት ተጠርጥረው ለእስር የተዳረጉ አባላት፣ ‹‹የፖለቲካ ታጋዮች እንጂ ሽብርተኞች አይደሉም›› ይላሉ፡፡

ግለሰቦቹ ፓርቲያቸውን ወክለው በሰጡዋቸው ኢንተርቪዎችና በጻፉዋቸው ምክንያት መከሰሳቸውን ገልጸው፣ በትክክል አሸባሪ ሆነው ከተገኙ፤ ፓርቲውም ‹‹አሸባሪነት የሚያራምድ›› ተብሎ ሊጠየቅ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

ዶክተር ነጋሶ እንደሚሉት፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ሆነው የተናገሩት ነገር፤  ፍርድ ቤቱ ሥራውን ነፃ ሆኖ እንዳይሰራ  ትዕዛዝ ከማስተላለፍ የሚተናነስ አይደለም፡፡ የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥትን ወክለው ሲናገሩ የሚጠቀሙዋቸው ቃላቶች በፍርድ ሒደት ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የተገነዘቡ አይመስለኝም ይላሉ፡፡

‹‹እርግጠኞች ነን፣ አሸባሪ ስለመሆናቸው መረጃዎች አሉን፤›› ማለት፤ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው ያሉት አቶ ሙሼ፣ “ማስረጃ ካላቸው ማቅረብ ያለባቸው ለፍርድ ቤቱ እንጂ፤ ለሕዝብ አይደለም”ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርግጠኛ የሆኑበትን ጉዳይ ዳኛ “አይደለም” ብሎ ለመፍረድ እንደሚቸግር የሚናገሩት አቶ ሙሼ፣ ‹‹አንዳንድ መሻሻሎች ቢኖሩም፤ ዳኞች ከማናቸውም  የፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ናቸው የሚባልበት ሁኔታ ላይ አልደረሰንም፤›› ብለዋል።